ለ30 ተቋማት ነጻ የዳታ ማዕከል አገልግሎት እየተሰጠ ነው – ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለ30 የመንግስት ተቋማት ነጻ የዳታ ማዕከል አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተ ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እንዳሉት ÷ በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቋማት ዳታን በአግባቡ ጥቅም ላይ የማዋል ልምዳቸው አነስተኛ ነው፡፡
በሌላ በኩል ዳታን በትክክል የማስቀመጡ ተሞክሮ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው÷ያለውን ዳታ ተረድቶ በአግባቡ የመጠቀም ችግር በሰፊው እንደሚስተዋልም አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ ግን ከተቋማት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ አብዛኛዎቹ ተቋማት ዳታን በአግባቡ እንዲያስቀምጡ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን (“ኤአይ”) በመጠቀም ተቋማቸውን ማዘመን እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለዚህም ለ30 ተቋማት በነጻ የዳታ ማዕከል አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ከውጭ ሀገራት በተለይ ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና ከእስራኤል ተቋማት አጫጭር ስልጠናዎች መገኘቱንም ጠቅሰዋል፤፤
ዳታ ለአንድ ሀገር ትልቅ ሃብት መሆኑን በመገንዘብ በአግባቡ ማስቀመጥ እና ጥቅም ላይ ለማዋል በትብብር መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአመለወርቅ ደምሰው