Fana: At a Speed of Life!

10 ነጥብ 7 ሚሊየን የኢትዮ ቴሌኮም የአክሲዮን ድርሻዎች ተሽጠዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ አክሲዮን ሽያጭ 10 ነጥብ 7 ሚሊየን የአክሲዮን ድርሻዎች መሸጣቸውን ኢትዮ ቴሌኮም አስታወቀ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የ10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፤ በመንግስት አካታች ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት በርካታ ሥራዋችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

ከእዚህ መካከል አንዱ የካፒታል ገበያ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም መሠረት ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ባለድርሻነት ተይዞ የነበረውን ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶው ለዜጎች እንዲተላለፍ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም የአክሲዮን ሽያጭ ይፋ መደረጉን አስታውሰዋል።

ከጥቅምት 7 እስከ ታህሳስ 25 ቀን 2017 የመጀመሪያው ዙር ሽያጭ መደረጉን ጠቅሰው፤ በርካቶች ባቀረቡት የይራዘም ጥያቄ መሰረት እስከ የካቲት 7 ቀን 2017 ሁለተኛው ዙር የአክሲዮን ሽያጭ ተከናውኗል ብለዋል።

ለ121 ቀናት በዲጂታል አማራጭ ጭምር በተካሄደው የኢትዮ ቴሌኮም የ10 በመቶ የአክሲዮን ሽያጭ 47 ሺህ 377 ኢትዮጵያዊያን መሳተፋቸውን ገልጸው፤ በዚህም 10 ነጥብ 7 ሚሊየን የአክሲዮን ድርሻዎች ተሽጠው 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የተከፈለ ገንዘብ ተሰብስቦ በዝግ አካውንት መቀመጡን ተናግረዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ባለ አክሲዮን የሆናችሁ 47 ሺህ 377 ኢትዮጵያዊያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

አሁንም በርካታ የአክሲዮን ግዢ ጥያቄ መኖሩን ገልጸው፤ የቀሩ አክሲዮኖችን በተመለከተ መንግስት በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት ወደ ፊት ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በፈቲያ አብደላ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.