በመዲናዋ የነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከነዳጅ አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኳንንት (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ሀቢባ ሲራጅና የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ተገኝተዋል።
አቶ ጃንጥራር አባይ በዚህ ወቅት ÷ የነዳጅ አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ማወቅ መፍትሄ ለመስጠት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አንስተዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት መሠረት ያደረገ የነዳጅ አቅርቦት መኖሩን ጠቅሰው÷ የሀገር ሃብት የሆነውን ነዳጅ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት በሚቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል ያሉት ም/ከንቲባው÷ እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ ለመሸጥ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በመዲናዋ ለሚስተዋለው የነዳጅ አቅርቦት እጥረት መንስኤ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ÷ከነዳጅ ሥርጭት ጋር ተያይዞ በማደያዎች የሚፈፀሙ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን አስረድተዋል፡
ችግሩን ለመፍታት ቢሮው የሚያከናውነውን የቁጥጥር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
ደስታው መኳንንት (ዶ/ር) ÷ መንግሥት ለነዳጅ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ነዳጅን ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በየደረጃው ያለውን ሌብነት ማስቆም እና አስተማሪ ርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በየሻምበል ምህረት