ሊቨርፑል ሻምፒየንነቱን ቀድሞ ለማረጋገጥ አንድ ነጥብ ብቻ…
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ34ኛ ሣምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የሊጉ መሪ ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ሮድ ምሽት 12 ሠዓት ከ30 ቶተንሃም ሆትስፐርን ያስተናግዳል።
ሊጉን በ79 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል ከዛሬው ጨዋታ አንድ ነጥብ ካገኘ ቀሪ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ሻምፒየን መሆኑን ያረጋግጣል።
ተጋጣሚው ቶተንሃም ሆትስፐር በበኩሉ፤ በሊጉ የደረጃ ሠንጠረዥ በ37 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስበርስ ግንኙነቶች ሊቨርፑል በሦስቱ ሲያሸንፍ፤ ቶተንሃም በሁለቱ ድል አድርጓል።
ሊቨርፑል በሊጉ ተከታታይ ሦስተኛ ጨዋታውን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ ሲገባ፤ ቶተንሃም ደግሞ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል።
በሌላ የሊጉ ጨዋታ ቀን 10 ሠዓት ላይ ማንቼስተር ዩናይትድ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከበርንማውዝ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል።
ማንቼስተር ዩናይትድ በ38 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በርንማውዝ በበኩሉ በ49 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ቀያይ ሰይጣኖቹ በሁሉም ውድድር ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት በአንዱ ብቻ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ካደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስበርስ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁለት ሁለት ጊዜ ድል ሲቀናቸው በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።
በዚህ የውድድር ዓመት በኦልድትራፎርድ ባደረጉት የመጀሪያ ዙር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በርንማውዝ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
በዛሬው ጨዋታ የሚያሸንፈው ቡድን ነጥቡን ከፍ በማድረግ ደረጃውን ማሻሻል ይችላል።
በወንድማገኝ ፀጋዬ