ማንቼስተር ዩናይትድ ለአውሮፓ መድረክ…
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዩሮፓ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ አትሌቲክ ቢልባኦ ከማንቼስተር ዩናይትድ እንዲሁም ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከቦዶ ግሊምት ይገናኛሉ።
በውድድር ዓመቱ በፕሪሚየር ሊጉ በ15 ጨዋታዎች ተሸንፎ መጥፎ ሪከርድ የተመዘገበበት ዩናይትድ፥ በተቃራኒው በአውሮፓ መድረክ ምንም ሽንፈት ያላስተናገደ ብቸኛው ክለብ ነው።
ዩናይትድ ለቀጣይ ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ለማግኘት የቀረው ብቸኛ እድል የዩሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ ሲሆን፥ ዛሬ ወደ ስፔን ተጉዞ አትሌቲክ ቢልባኦን ይገጥማል።
ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሚደረገው የግማሽ ፍጻሜው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ማንቼስተር ዩናይትድ በመድረኩ ያለመሸነፍ ግስጋሴውን ያስቀጥላል ወይስ የመጀመሪያ ሽንፈቱን ያስተናግዳል የሚለው ይጠበቃል።
ፖርቹጋላዊው የማንቼስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም፥ “የዩሮፓ ሊጉን ዋንጫ ማሳካት የሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ከማግኘት በተጨማሪ ለኛ ትልቅ ትርጉም አለው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
በሌላ የግማሽ ፍጻሜ መርሐ ግብር በተመሳሳይ በፕሪሚየር ሊጉ ደካማ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ቶተንሃም ሆትስፐርስ ሳይጠበቅ ለግማሽ ፍጻሜ የደረሰውን የኖርዌዩ ቦዶ ግሊምት በሜዳው ያስተናግዳል።
በሌላ በኩል በዩሮፓ ኮንፈረንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ቼልሲ ከሜዳው ውጭ ከስዊድኑ ዩርጋደን እንዲሁም ሪያል ቤቲስ ከፊዮሬንቲና ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይገናኛሉ።