ኢትዮጵያ በክህሎት ልማት ሁለተኛውን የዓርበኝነት ምዕራፍ ጀምራለች – ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በክህሎት ልማት ሁለተኛውን የዓርበኝነት ምዕራፍ መጀመሯን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ኢትዮ ክህሎት 4ኛው ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር “ብሩህ አዕምሮዎች በክህሎት የበቁ ዜጎች” በሚል መሪ ሃሳብ ከሚያዝያ 27 እስከ ግንቦት 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪሃት መርሐ ግብሩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ÷ ኢትዮ ክህሎት ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር የስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ በየሁለት ዓመቱ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሲካሄድ በቆየው ውድድር አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች የሚሳተፉበት የክህሎትና የቴክኖሎጂ ውድድር መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የክህሎት ውድድሩ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ እና ከገበያው ፍላጎት ጋር የሚያስተሳስሩ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ጠቁመዋል።
ውድድሩ በ22 ዘርፎች እንደሚካሄድና የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት የሚያስችል መርሐ ግብር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያን በዘርፉ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ጠቅሰው÷በውድድሩ 70 አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለእይታ ይቀርባሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት 81 ቴክኖሎጂዎች መልማታቸውንና በዘንድሮው በጀት ዓመት ደግሞ 180 ተሳታፊዎች 99 ቴክኖሎጂዎች በማልማት ሒደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የዓርበኝነት ምዕራፍ ጀምራለች ያሉት ሚኒስትሯ÷ የክህሎት ውድድሩ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።