የቱሪዝም ዘርፍን በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ይሰራል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
ሐረር ከተማ የዓለም የቱሪዝም ከተሞች አባል መሆኗን በማስመልከት የማብሰሪያ መርሐ ግብር በተካሄደበት ወቅት፤ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት÷ ለቱሪዝም ዘርፍ በተሰጠው ትኩረትና በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም ከለውጡ ወዲህ በተሰሩ ሥራዎች ሐረር ከተማና በውስጧ የሚገኙ ቅርሶች ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበችው ሐረር ከተማ 115 አባል ሀገራትን በያዘው የዓለም የቅርስ ከተሞች ድርጅት ውስጥ በአባልነት መመረጧን አስታውሰዋል።
በተጨማሪም የሹዋሊድ በዓል አከባበር በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡
ሐረር የዓለም ቱሪዝም ከተሞች ፌዴሬሽን አባል ሆና መመረጧም የቱሪዝም መዳረሻነቷን ለማሳደግ እንደሚያግዝ የገለጹት አቶ ኦርዲን በድሪ፤ ከሌሎች አቻ ከተሞች ጋር ትስስር መፍጠር አብሮ ለመስራትና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የላቀ ነው ብለዋል።
በዚህም ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት በማጠናከር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በተስፋዬ ሀይሉ