በ4 ክልሎች ለባሕላዊ ፍ/ቤቶች እውቅና የሚሰጥ አዋጅ ጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአራት ክልሎች ለባሕላዊ ፍርድ ቤቶች እውቅና የሚሰጥ አዋጅ መጽደቁን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ እንደገለጹት÷ ባለፉት ጊዜያት የፍትሕ ሥርዓቱን ማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ ሪፎርሞች ተከናውነዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በአማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና ሲዳማ ክልሎች ለባሕላዊ ፍ/ቤቶች እውቅና የሚሰጥ አዋጅ መጽደቁን ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ፈተናዎች መካከል ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓቱ ከውጪ መቀዳቱ አንዱ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ÷ ችግሩን ለመቅረፍ የመሰረተ ማሕበረሰብ ፍትሕ ሥርዓት መተግበር መጀመሩን ጠቅሰዋል።
የመሰረተ ማሕበረሰብ ፍትሕ ሥርዓት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የእርቅ እና ሸንጎ ሥርዓቶችን መሰረት አድርጎ ሕጋዊ መልክ የያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ላይ የሚነሡ ክፍተቶችን እንደሞላ ጠቁመው÷ እነዚህን መልካም ተሞክሮዎች ለማስፋት ባሕላዊ ፍ/ቤቶችን ማቋቋም የሚያስችል ጥናት በተለያዩ ክልሎች እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት የመሰረተ ማሕበረሰብ ፍትሕ ሥርዓትን ለማጠናከር 7 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
በቃለአብ ግርማ