Fana: At a Speed of Life!

በእስራኤል የተከሰተው ሰደድ እሳት በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በእስራኤል የተከሰተው ሰደድ እሳት ከ30 ሰዓታት የእሳት አደጋ ሰራተኞች ብርቱ ትግል በኋላ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡

በአደጋው በርካታ የኢየሩሳሌም ከተማ አቅራቢያ ነዋሪዎች የተፈናቀሉ ሲሆን÷12 ሰዎች ደግሞ ከሰደድ እሳቱ በሚወጣው ጭስ ሳቢያ የመተንፈስ ችግር አጋጥሟቸው ሆስፒታል መግባታቸው ተመላክቷል፡፡

የእስራኤል እሳት አደጋ ባለስልጣን እንዳስታወቀው÷ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ ያካለለው ሰደድ እሳት ወደ እስራኤል መዲና ተስፋፍቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

በእሳት ማጥፋት ዘመቻው የጣልያን፣ ክሮሺያ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ዩክሬንና ሮማኒያ የእሳት አደጋ ሠራተኞች  መሳተፋቸው ተጠቁሟል፡፡

ሰደድ እሳቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተከትሎ ከቴል አቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደው ዋና መንገድ  ለአገልገሎት ክፍት መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ÷የሰደድ እሳቱን መነሻ ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

ትዕዛዙን ተከትሎ በተደረገ ምርመራም የሀገሪቱ ፖሊስ በሰደድ እሳቱ መከሰት የተጠረጠሩ 18 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል፡፡

እስራኤል በታሪኳ ከፍተኛ የሰደድ እሳት አጋጥሟት የነበረው በፈረንጆቹ 2010 ሲሆን÷በወቅቱ 12 ሺህ ሄክታር ያቀጣለው ሰደድ እሳት 44 ሰዎችን ደግሞ ለሕልፈት መዳረጉን አሶሼትድ ፕሬስ በዘገባው አስታውሷል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.