Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፖስታ አገልግሎት እየሰጠች ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከለውጡ ወዲህ በዘርፉ በተከናወኑ የማሻሻያ ሥራዎች በፈጣን መልዕክት አገልግሎት ቀዳሚ ከሆኑ አስር ሀገራት ተርታ መሰለፍ መቻሉን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዳግማዊ ኃይልዬ እንዳሉት÷ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተካሔደው የሪፎርም ሥራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፖስታ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በፈጣን መልዕክት የፖስታ አገልግሎት ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደነበረች አስታውሰዋል።

በዋናነት በጥናት ላይ የተመሰረቱ ማሻሻያዎች በመደረጋቸው ሰፊ ለውጥ በማምጣት ድርጅቱን በፈጣን መልዕክት አገልግሎት ቀዳሚ ከሆኑ አስር ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ተችሏል ነው ያሉት።

በፋይናንስ በኩል ሪፎርሙ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ተቋሙ ኪሳራ ውስጥ እንደነበር ገልጸው÷ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሁለንተናዊ የለውጥ ሥራዎች ትርፋማ መሆን ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በየዓመቱ እድገት በማስመዝገብ የተቋሙን ገቢ ከለውጡ በፊት ከነበረው አፈፃፀም ከሰባት እጥፍ በላይ ማሳደግ እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

ድርጅቱ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ስትራቴጂ በመቅረጽ ያከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች በዘርፉ ለውጥ እንዲያመጣ አድርጓል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የመልዕክት ደህንነትን በሚገባው ደረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ጠቅሰው÷ በፖስታ አገልግሎት የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ከመሰረታቸው ለመፍታት አበክረን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 190 መዳረሻዎች እንዳሉት መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.