Fana: At a Speed of Life!

መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ኃላፊነቱን የሚወጣ የፖሊስ ሠራዊት ተፈጥሯል – ኮ/ጄ ደመላሽ ገ/ሚካኤል

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የሚሰጠውን ኃላፊነት የሚወጣ የፖሊስ ሠራዊት ተፈጥሯል ሲሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

116ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ምሥረታ ቀን የማጠቃለያ መርሐ ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው።

ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት፥ በለውጡ የተደራጁ የተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር የተሰጠውን ኃላፊነት የሚወጣ ሠራዊት መፈጠሩን ተናግረዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ከተጣለ ጀምሮ የፌደራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመሆን 24 ሰዓት የግድቡን ደህንነት ሲጠብቅ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

የኮስታል ፖሊስ ጋርድ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ መደራጀቱን ጠቅሰው፥ በቀጣይም ከመንግስት በሚሰጠው ተልዕኮ እንደሚሰማራ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነር ጄነራሉ የዲኤንኤ ምርመራን በማስጀመር አሁን ላይ ተቋሙ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝና በቅርቡም ዓለም አቀፍ የፖሊስ አመራር ማዕከል ወደ ስራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የፌደራል ፖሊስ የዜጎች መተግበሪያ (EFPApp) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳድሮ ምርጥ የፖሊስ መተግበሪያ በመባል በአንደኛ ደረጃ ማሸነፉን አብስረዋል፡፡

ተቋሙ የፖሊስ የድሮን ሃይል፣ ዲጂታል የመገናኛ ሬዲዮ፣ የኮማንድ ኮንትሮል ማዕከልና ዘመናዊ የሎጂስቲክስ አቅሞች ባለቤት መሆኑን አንስተው በቀጣይ ሌሎች የቴክኖሎጂ አቅሞችን ለማስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለተቋሙ ለሰጡት ትኩረትና ጠንካራ አመራር ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ምስጋና አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.