የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ብቁ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ መፍጠር ይገባል – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ዘመኑን የዋጀ ብቁ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ መፍጠር ይገባል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
’’የድህረ እውነት ዘመን በእውነትና በእውቀት’’ በሚል መሪ ሐሳብ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራሮችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በጋምቤላ ከተማ እየተሰጠ ነው።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በስልጠና መድረኩ ላይ፤ በድህረ እውነት ዘመን በእውነትና በእውቀት የሚመራ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ ለህዝቦች አንድነትና ለሀገር ዕድገት አዎንታዊ ሚና አለው ብለዋል።
በመሆኑም የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ በቅጡ በመረዳት ዘመኑን የዋጀ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ መፍጠር ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።
ለዚህም የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በእውነትና በእውቀት ላይ በመመስረት ከዲጂታሉ ዓለም ጋር በመራመድ ፈጣንና ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ መሆን እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዳበረ ኢኮኖሚ ለመገንባት፣ ማህበራዊ ፍትህ ለማስፈንና እውነተኛ ዴሞክራሲ ለማረጋጥ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት በለውጡ የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶችን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ የእነዚህን አካላት ሴራ በማክሸፍ እውነተኛ መረጃዎችን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሺኔ አስቲን፤ የተቀናጀና የተደራጀ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ የተጀመረውን የለውጥና የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ ከሚዲያው እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።