የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም (ሊያንዩንጋንግ) የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆና መመረጧ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በዚሁ ወቅት፤ ፎረሙ በመተባበር የጋራ ደኅንነትን በማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃ የሕዝቦችን ደኅንነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ትገኛለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ትብብሩ ይበልጥ እንዲጠናከር ኢትዮጵያ የምታበረክተውን አስተዋጸኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
የዓለም አቀፍ የሕዝብ ደኅንነት ትብብር ፎረም ሊቀ መንበር (ሊያንዩንጋንግ) አንዲ ትሳንግ በበኩላቸው፤ ፎረሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግጭቶችንና ዋና መንስኤዎችን ለማስወገድ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ ለመግታት እየተሠራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡