የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ያልያዘ አሽከርካሪ ማሽከርከር አይችልም- ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከያዝነው ዓመት ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአሽከርካሪዎች የሙያ ብቃት ምዘና እንደሚጀመር የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የብቃት ምዘናውን መስጠት ያስፈለገው 83 በመቶ በሀገሪቱ እየደረሰ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ ከአሽከርካሪዎች እና ተሽከርካሪዎች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
ይህን ተከትሎም በዚህ ዓመት ምዘናው ሥራ ላይ ባሉ አሽከርካሪዎች እንደሚጀመር የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ አማካሪ አሰፋ ሀዲስ አረጋግጠዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በሕዝብ እና ደረቅ ጭነት ከ1 እስከ 3 ባሉ ደረጃዎች እንዲሁም ለፈሳሽ 1 እና 2 አሽከርካሪዎች የሙያ ብቃት ምዘና እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡
የሙያ ብቃት ምዘና ከመሰጠቱ በፊት ለአሽከርካሪዎቹ የሙያ ስልጠና እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡
ከስልጠናው በኋላ የሙያ ብቃት ምዘና (ሲኦሲ) እንደሚወስዱ እና ፈተናውን ያለፉት መንጃ ፈቃዳቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የሙያ ብቃት ምዘና ፈተናውን ወስደው ያላለፉ አሽከርካሪዎች እንደገና ስልጠና ወስደው ድጋሚ ይፈተናሉ ብለዋል፡፡
የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ያልያዘ አሽከርካሪ ማሽከርከር እንደማይችልም ነው ያሳሰቡት፡፡
በቀጣይም የሙያ ብቃት ምዘናው ታክሲን ጨምሮ በሌሎቹም አሽከርካሪዎች ላይ እንደሚተገበር ጠቁመዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ