በትግራይ ክልል የኃይል ተደራሽነትን ለማሳደግ የማስፋፊያ ሥራ እየተከናወነ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የመቐለ ሪጅን እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማስተናገድ የሚያስችል የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት የማስፋፊያ ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ወራትም 175 ነጥብ 92 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም 135 ነጥብ 14 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ ማከናወኑን ለፋና ዲጂታል አስታውቋል፡፡
በዓዲግራት ፋፂ፣ ዕዳጋ ሓሙስ፣ ፍረዎይኒ፣ ሓውዜን ውቅሮ፣ አጉላዕ እና አፅቢ፤ ለመንደር ማስፋፊያ፣ ለመስኖ ልማት፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት ሥራ እንዲሁም ለተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ተግባራት እና ቱሪዝም ገበያ ማዕከላት ግንባታ አገልግሎት የሚሰጡ 198 የተለያየ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮች ተከላ ተከናውኗል ብሏል፡፡
የማስፋፊያ ሥራው አካባቢዎቹ ላይ በአነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች የተሰማሩ ማኅበራት እና ሥራ ፈጣሪ ኢንተርፕራይዞችን እንዲሁም አዳዲስ አምራች ተቋማትና አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በርካታ የመስኖ ልማት፣ የከርሰ ምድር ውኃ፣ የመኖሪያ ቤቶች መንደር ማስፋፊያ፣ ለተለያዩ የኢንቨስትመንትና ሕዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል 21 ነጥብ 34 ኪሎ ሜትር መካከለኛ መስመር፣ 59 ነጥብ 47 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ እንዲሁም 201 ትራንስፎርመሮች ተከላ በክልሉ ደቡባዊ እና ደቡብ ምሥራቅ ዞን ከተሞች አካባቢዎች ለማከናወን እየተሠራ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
በዮሐንስ ደርበው