ሠላምን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ የዜጎች ሚና የጎላ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሠላምን ለማረጋገጥ በሚሠራው ሥራ ዜጎች የጎላ ሚና እንዳለቸው ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) አሳሰቡ፡፡
በክልሉ ማኅበረሰቡን የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ ያለሙ ውይይቶች ተደራሽ ያልነበሩትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እየተካሔዱ መሆናቸውን ኃላፊው ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡
የውይይቶቹ ተሳታፊዎችም፤ የግጭትን አክሳሪነት አንስተው ሕግ የማስከበሩ ሥራ እንዲጠናከር መጠየቃቸውን እና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደርጉ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
የተስተጓጎሉ አገልግሎቶች ወደ ቀደመ ተግባራቸው እንዲመለሱላቸው ለማድረግ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙም ገልጸውልናል ብለዋል፡፡
የልማት ሥራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የጠቅሱት ኃላፊው፤ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ቀበሌዎች ወርደው ከማኅበረሰቡ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት የሰላም በሮች አሁንም ክፍት መሆናቸውን በመገንዘብ በዕድሉ መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበው፤ ከዚህ ውጭ ላሉ እንቅስቃሴዎች ግን ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሰለሞን ይታየው