Fana: At a Speed of Life!

ሽብርተኝነትን በመከላከል የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ይገባል -አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሽብርተኝነት እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በብቃት በመከላከል የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሀገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

የአፍሪካ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ስብሰባ “በመረጃ ትብብር የቀጣናውን ደህንነት ማጠናከር” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በስብሰባው ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ኮሚቴ አባል ሀገራት፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በወቅቱ እንዳሉት፤ ሽብርተኝነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣ የሳይበር ጥቃት እና ግጭት የቀጣናው ስጋት ሆነው ቀጥለዋል።

በቀጣናው የሚስተዋለውን የጸጥታና ደህንነት ስጋት በብቃት ለመመከት በሀገራት የጸጥታ ተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ጠንካራ ትብብር በመፍጠር የቀጣናውን ሰላምና ጸጥታ ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

ሽብርተኝነትና ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከል የሚያስችል ሪፎርም ያደረገው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሆነም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ተወካይና የሕብረቱ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር መሀመድ አል አሚን ሱዌፍ ስብሰባው በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ለመምከር ወሳኝ ሰዓት መሆኑን ገልጸዋል።

የሳይበር ጥቃት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ሽብርተኝነትን ለመከላከል በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

ለዚህም በቀጣናው ሀገራት መካከል የተሳለጠ የመረጃ ልውውጥ ሊኖር እንደሚገባ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.