Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ሚናዋን አዘምና እንደምትቀጥል አረጋገጠች

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደኅንነት ማስከበር ያላትን ዘመናት የተሻገረ ሚና በይበልጥ በማዘመን አጠናክራ እንደምትቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) አረጋገጡ፡፡

በሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) የተመራ ልዑክ በበርሊን እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡

ይህን አስመልክቶ የመከላከያ ሚኒስትር አማካሪ ስመኝ ግዛው ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት፤ ሚኒስትሯ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ከተቀላቀለችበት ጊዜ አንስቶ ቀዳሚ አስተዋፅዖ እያበረከተች መሆኗን አንስተዋል፡፡

በቀጣይም ይህንን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነች መሆኗን አረጋግጠዋል ነው ያሉት፡፡

በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ፤ የፋይናንስ ድጋፍ መቀነስ፣ የሰላም ማስከበር የአፈጻጸም ጥራት እና ታማኝነት መጓደል፣ ሰላም ማስከበር የሚካሄድባቸው ሀገራት ተሳትፏቸውን ማጉላት አለመቻላቸው የሚሉትን እንደ ተግዳሮት ጠቅሰው፤ መፍትሔ እንዲበጅላቸው መጤቃቸውንም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ በዲስፕሊን፣ በቁርጠኝነትና ሙያዊ ብቃታቸውን በማስመስከር፣ ከሕዝብ ጋር ከፍተኛ ትስስር በመፍጠር ግዳጃቸውን እየፈጸሙ አኩሪ ስም ማትረፋቸውንም ገልጸዋል ብለዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.