Fana: At a Speed of Life!

ቀጣናው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በመገምገም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ከስምምነት ተደረሰ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቀጣናው ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በመገምገም ተግባራዊ እርምጃዎች ለመውሰድ ከስምምነት መደረሱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል ታዜር ገ/እግዚአብሔር በሰጡት መግለጫ “በመረጃ ትብብር የቀጣናውን ደኅንነት ማጠናከር” በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት ተቋማት ጉባዔ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው የአንድ ሀገር የፀጥታ ችግር የእዛ ሀገር ብቻ አይደለም የሚለው ሐሳብ የጉባዔው ትኩረት ከነበሩ ነጥቦች መካከል አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ አግባብም የፀጥታ ችግሮችን ለመከላከል በጋራ የመሥራት ሁኔታ ወሳኝ መሆኑ በሀገራቱ ዘንድ ከስምምነት ተደርሶበታል ነው ያሉት፡፡

በሀገራቱ የደኅንነት ተቋማት መካከል፤ የደኅንነት ስጋቶችን ቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የመረጃ ልውውጥ እንዲኖርም ከመግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

በጉባዔው ላይ ከአፍሪካ፣ እስያና አውሮፓ የተውጣጡ ከ30 በላይ ሀገራት መሳተፋቸውንም በመግለጫቸው ጠቅሰዋል፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች የሕዳሴ ግድብን መጎብኘታቸውን እና ይህም አፍሪካውያን ከተባበሩ እንደዚህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክት መፈፀም እንደሚችሉ ለማመልከትና በግድቡ ዙሪያ የሚነዙ ስሁት መረጃዎችን ለማጥራት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ የልማት ሥራዎችን በመጎብኘት ተሞክሮ መቅሰማቸውን አንስተዋል፡፡

በአጠቃላይ ጉባዔው ሀገራችንና ተቋማችን በምሥራቅ አፍሪካ ያላቸውን ገፅታ ለማስተዋወቅ ያገዘ ነበር ብለዋል፡፡

በአንዱዓለም ተስፋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.