Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ድህነትንና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ የተግባር ቁርጠኝነትን ማጠናከር ይገባል – አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ድህነት፣ ሥራ አጥነትና አድሏዊነትን ለመቅረፍ የሀገራት የተግባር ቁርጠኝነትና ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ፡፡

20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት በሥራ ላይ የተመሰረተ የባለሙያዎች ‘ሌቨር ቤዝድ ፕራክቲሽነርስ’ አህጉራዊ ስብሰባ በአፍሪካ ሕብረት እየተካሄደ ነው።

አፈ-ጉባዔ ታገሰ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ ስብሰባው አፍሪካውያን ፖሊሲ አውጭዎችና ባለሙያዎች ፈጠራን መሰረት ያደረገ ስራ ለመፍጠር፣ ድህነትን ለመቀነስና አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

አላማውን ለማሳካትም በአህጉሪቱ የሁሉም ሀገራት የጋራ ጥረት ያስፈልጋል ያሉት አፈ ጉባዔው ÷ ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ ጥረት እንዲሁም ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል ነው ያሉት፡፡

ፖሊሲዎች፣ የልማት ስትራቴጂዎች እንዲሁም የመሰረተ ልማት ሃብቶች ለስራ እድል ፈጠራና ለአካታች ለውጥ መሰረት መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የልማት ግቦች ድህነትን ለመቀነስ፣ የሥራ እድል ለመፍጠርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋጥ የሚያስችሉ እንደሆነ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ሥብሰባ የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት የጋራ መፍትሔ የማስቀመጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

አፍሪካ ያሉባትን ፈተናዎችና ያሏትን መልካም እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም በትብብር ላይ የተመሰረተ የተግባር ድርጊት ያስፈልጋል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.