Fana: At a Speed of Life!

የኢጋድ አባል ሀገራት አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ለማመንጨት ጠንካራ ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል – ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ለማመንጨት የሚያስችል ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል ሲሉ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

የኢጋድ የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር 70ኛው የአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ምልከታ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።

ሃብታሙ (ዶ/ር ኢ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ በአፍሪካ ቀንድ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅና ጎርፍ በርካቶችን እየፈተነ ነው።

ግብርና፣ የምግብ ሉዓላዊነት፣ የውሃ ሀብት፣ ቱሪዝምና ጤና በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከሚደርስባቸው ዘርፎች በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ አስተማማኝና ትክክለኛ የአየር ትንበያ መረጃን ለመተንተንና ለማሰራጨት የሚያስችል የተቋም ማዘመንና ጠንካራ ሥርዓት የመዘርጋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢጋድ የአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል ወቅታዊና አስተማማኝ የአየር ጠባይ መረጃ በማቅረብ የአባል ሀገራቱ የዘርፉን ባለሙያዎች አቅም ለማጎልበት የሚሰራው ስራ የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።

በየሀገራቱና በአጠቃላይ በቀጣናው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ትክክለኛና አስተማማኝ የአየር ንብረት መረጃን ለማመንጨት የሚያስችሉ ስርዓቶችን ለመዘርጋት ኢንቨስት ማድረግ አለብን ብለዋል።

የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሀመድ አብዲ ዋሬ በበኩላቸው÷ በአፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ የተለያዩ አደጋዎችና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡

ኢጋድ በአየር ጠባይ ትንበያና ትግበራ ማዕከል በኩል ለቀጣናው የአየር ንብረት ትንበያ መረጃን ተደራሽ እያደረገ እንዲሁም ለሀገራቱ ድጋፍ እየሰጠ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ፥ መንግስት ኢንስቲትዩቱንና የክልል የሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላትን እያጠናከረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሙያተኞችን አቅም ለማሳደግና ዘመናዊ የሚቲዎሮሎጂ ምልከታ ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.