የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የጀርመን ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ትብብር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የጀርመን ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን በአፍሪካ የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር በትብብር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
የተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች በኮትዲቯር አቢጃን ባካሄዱት ውይይት፤ በአፍሪካ በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች፣ በታዳሽ ኃይል፣ በመሠረተ ልማት አውታሮች እና በአህጉሪቱ ኢንዱስትሪ ልማት ላይ የሚገኙ የግል ዘርፍ ተሳትፎዎችን ለማጠናከር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
በአፍሪካ ልማት ባንክ የግሉ ዘርፍ፣ መሠረተ ልማትና ኢንዱስትሪያላይዜሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሰለሞን ኩዋይኖር እንዳሉት፤ ትብብሩ የግሉ ዘርፍ ለአፍሪካ ልማትና እድገት አስተዋፅዖ እንዲያደርግ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡
ተቋማቸው ለግሉ ዘርፍ አዳዲስ ዕድሎችን እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአህጉሪቷን ችግሮች በመቅረፍ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ይረዳል ማለታቸውን የባንኩ መረጃ አመላክቷል፡፡
የጀርመን ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሮላንድ ሲለር በበኩላቸው፤ ከባንኩ ጋር ያላቸው ትብብር ጀርመን ለምትከተለው የአፍሪካ ስትራቴጂ መሠረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከልማት ባንክ ጋር በትብብር በመሥራት በአህጉሪቱ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን መፍጠር እንችላለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ