ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የተሰጠ ወቅታዊ መረጃ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሞኑን የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ በሀገራችን ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር በማበር ሕገ ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፣ በጤና ዘርፉ ላይ ሁከት በመፍጠር እና የታካሚዎችን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል የተጠረጠሩ 47 የጤና ባለሙያዎችን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ ማጣራት ጀምሯል፡፡
እነዚህ ተጠርጣሪዎች የጤና ባለሙያዎች ያነሱትን የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ እንደሽፋን በመጠቀም ሕገ-ወጥ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ፤ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ለአድማ በማነሳሰት፣ የታካሚዎች ሕይወት ለሞትና ለአደጋ እንዲጋለጥ በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር የተጠረጠሩ ናቸዉ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተለያዩ የጤና ተቋማት የአድማ መረቦችን በመዘርጋት፤ የጤና ባለሙያ ያልሆኑ አካላትን ነጭ ጋዋን በማስለበስ የሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ገብተዉ ሁከት እንዲፈጥሩ በማድረግ፣ ያልተገባ ወሬ በመንዛት እና በተለያየ መንገድ ሰላማዊ የሕክምና ሂደትን በማደናቀፍ የሕሙማንና የጤና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ፣ በመንግሥት የሕክምና አገልግሎት እና ትምህርት በሚሰጥባቸው ተቋማት ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲስተጓጎል አድርገዋል፡፡
እንዲሁም ሙያቸውን አክብረው በሥራ ላይ በተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት ከማድረስ ባለፈ ሁከት እንዲፈጠር ሙከራዎችን አድርገዋል ያላቸውን 47 ተጠርጣሪዎች በመረጃና በማስረጃ በመለየት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የጤና ባለሙያዎቹ የሙያው ሥነ-ምግባርና ሕግ በማይፈቅደው ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት ለሞትና ለአደጋ በማጋለጥ ሥራ ማቆም፣ ሌሎችም ሥራ እንዲያቆሙ ማነሳሳት እና ማስፈራራት፣ የወንጀል ተግባር መሆኑን እየገለፀ ሌሎችም ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ ያሳስባል።
በዚህ አጋጠሚ ሕዝባቸውን እና ሕግ አክብረው አገልግሎት እየሰጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግ እያረጋገጠ፤ ከዚህ ውጭ ሁከትና ብጥብጥን ለማስፋፋት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ፖሊስ እየወሰደ ያለውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያሳውቃል።