Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከተለችው አቅጣጫ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል – ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገው ጥረትና በግብርናው ዘርፍ እየተከተለች ያለው የፖሊሲ አቅጣጫ ተጨባጭ ለውጥ ማስገኘቱን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለፁ።
ሚኒስትሩ ከፌዴራልና ከክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ቅንብቢትና ጅዳ ወረዳዎች ከ200 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በበጋ መስኖ እየለማ የሚገኝ የስንዴ እና የገብስ ማሳን ተመልክተዋል።

ጉብኝቱን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም፥ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ የብዝኃ ዘርፍ ልማት አቅጣጫን እየተከተለች መሆኗን አንስተዋል።

ሀገሪቱ በግብርና ምርታማነት በተለይም በስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ጤፍና ሩዝ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝም አስረድተዋል።

የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ የሚታረስ መሬትን መጨመር፣ በሄክታር የሚገኝ ምርትን ማሳደግና የምርት ወቅትን በመጨመር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየተዘመገበ ነው ብለዋል።

በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ በተመዘገበው ስኬት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከማስቀረት ባለፈ ለውጭ ገበያ ወደ መላክ መሸጋገር ተችሏል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተመለከቱት የመስኖ ስንዴ ልማት አስደናቂ እንደሆነም ጠቅሰው፤ ከዚህ ቀደም ቀለብ እየተሰፈረላቸው ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት የአካባቢያቸውን አቅም በመጠቀም ከተረጅነት ተላቀው ለገበያ እስከማቅረብ ደርሰዋል ብለዋል።

በጉብኝታቸው አርሶ አደሩ ሀገር በቀል እውቀቱን ተጠቅሞ ወንዞችን እየገደበ በርካታ ማሳ ማልማት መቻሉን ማረጋገጣቸውንም ተናግረዋል።

ይህም በግብርናው መስክ የተቀመጡ አቅጣጫዎች በስኬታማነት መተግበራቸውን እንደሚያሳይ አንስተዋል።

አክለውም ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እና ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር ያስቀመጠችው የልማት አቅጣጫ በትክክለኛ መንገድ ላይ ስለመሆኑ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

መንግሥት የመስኖ ልማትና የሌማት ትሩፋትን ማጠናከር፣ አገልግሎትን ማሻሻል፣ ምርታማነትን ማሳደግና ዘላቂ ሰላምን መገንባት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

ህብረተሰቡም ዘላቂ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎችን በባለቤትነት ማሳካት እንዳለበት ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.