Fana: At a Speed of Life!

በህፃን ባምላክ ግርማ ላይ ግድያ የፈፀሙት እናቷ እና የእንጀራ አባቷ በሞት እንዲቀጡ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቅጣት ዉሳኔዉን ያሳለፈዉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድሬዳዋ ምድብ 4ኛ የወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነዉ፡፡

ተከሳሾቹ ሀና በየነ እና ብሩክ አለሙ ላይ ዐቃቤ ሕግ አራት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን በአንደኛ ክስ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 539 (ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾች በጋራ በመሆን ሰውን ለመግደል በማሰብ ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከለሊቱ 5 ሰዓት በድሬዳዋ ከተማ 04 ቀበሌ ልዩ ቦታው ካባ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመኖርያ ቤታቸው ውስጥ የ1ኛ ተከሳሽ ልጅ እና የ2ኛ ተከሳሽ የእንጀራ ልጅ የሆነችውን የግል ተበዳይ ህፃን ባምላክ/ኬብሮን ግርማን ስለታማ ባልሆነ ቁስ ባደረሱባት ድብደባ የግንባሯን የግራ ጎን 6በ4 ሴ.ሜ፣ በግራ የዐይኗ ዐቃፊ ሶኬት ላይ 2በ1 ሴ.ሜ፣ በግራ ጉንጯ ላይ 6 ሴ.ሜ፣ በላይ እና በታችኛው ከንፍሯ ላይ 0.5በ0.5 ሴ.ሜ፣ በቀኝ ክንዷ ላይ 1በ0.5 ሴ.ሜ፣ በግራ ክንዷ የእጅ አምባር የፊተኛው ክፍል ላይ 1.5በ0.5 ሴ.ሜ፣ የታችኛው ከንፈር 3በ1ሴ.ሜ፣ በግራ ጀርባ የታችኛው ክፍል ላይ 5በ4 ሴ.ሜ ስፋት ያላቸው የመቁሰል፣ የመበለዝ እንዲሁም መጋጋጥ ጉዳቶች ውጫዊ አካሏ ላይ እንዲኖርባት በማድረጋቸው ምክንያት ከውስጣዊ አካሏ፣ አንጎል፣ ልብ፣ ጉበት፣ ጣፊያ፣ ቆሽት፣ ኩላሊት፣ የሽንት ማጠራቀሚያ ፊኛዋ ከመለስለሱ በተጨማሪ በማፈን አየር እንድታጣና ህይወቷ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ከባድ የግድያ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሁለተኛ ክስ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 375 (ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾች በጋራ በመሆን የሌላውን ጥቅም ወይም መብት ለመጉዳት ለራሳቸው ወይም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ ማንኛውንም መብት ወይም ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም የግል ተበዳይ አባት እውነተኛ ወላጅ አባቷ አቶ ግርማ አበጋዝ ሳይሆን 2ኛ ተከሳሽ እንደሆነ ሀሰተኛ የዲኤንኤ ማስረጃ በማሰራት ለፍርድ ቤት ሕጋዊ ክርክር ለማስረጃነት ለመጠቀም እንዲሁም የተለያዩ ሰዎችን ለማሳመን ያዘጋጁት በመሆናቸው ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በግዙፍ የሚፈፀም ሀሰተኛ ሰነዶችን መፍጠር ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በሶስተኛ ክስ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 585(2) (ሀ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾች በጋራ በመሆን ሕግን ተቃራኒ በሆነ መንገድ ወይም ያለ ሕጋዊ ትዕዛዝ የግል ተበዳይን ከመስከረም 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ግድያ እስከተፈጸመባት ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ወደ ወላጅ አባቷ እንዳትሄድ፣ በፍርድ በወንድሟ ላይ አልመሰክርም እንዳትላቸው ለማባበል እና ለማስፈራራት፤ ታማለች ጸበል እያስጠመቅናት ነው በማለት ትምህርት እንድታቋርጥ አድርገው ከሰው እንዳትገኛኝ ቤት ውስጥ ቆልፈውባት ያስቀመጧት በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከሕግ ውጪ ሰዎችን ይዞ ማቆየት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በአራተኛ ክስ ደግሞ በ1996 የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) ሀ እና 590(1) (ሐ) ሥር የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾች በጋራ በመሆን በሟች ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ሻወር በምትወስድበት ጊዜ ቪድዮ ቀርፀው ከግንቦት 2014 ዓ.ም ህይወቷ እስካለፈበት ጥቅምት 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እኛ የምንልሽን የማትሰሚ እና ከእኛ ጋር አርፈሽ ካልተቀመጥሽ፣ አባቴ እና ወንድሜ ጋር እሄዳለሁ ብለሽ የምታስቸግሪን ከሆነ ይሄንን ቪዲዮ ነው ለህዝብ አሳይተን ጉድሽን የምናፈላው እያሉ ሊጠብቋት፣ ሊንከባከቧት እና ፍቅር ሊሰጧት ሲገባቸው የተለየ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማስፈራራት በህፃኗ ነፃነት ጣልቃ ገብተው ከወላጅ አባቷ እና ከወንድሟ ጋር እንዳትገናኝ ያደረጓት በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የማስገደድ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ በተከሰሱባቸዉ አራቱም ክሶች ጥፋተኛ መሆናቸዉ በዐቃቤ ሕግ የሰዉና የሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ ችሎቱ በዛሬው ውሎ ተከሳሾቹ በሞት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡

በመቅደስ የኔሁን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.