Fana: At a Speed of Life!

ትግራይ ክልልን ወደ ግጭት ለማስገባት የሚጥሩ ጥቂት የቀድሞ ህወሓት አመራር አባላትን ሕዝቡ በቃችሁ ሊላቸው ይገባል- አቶ ጌታቸው ረዳ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልልን ዳግም ወደ ግጭት ለማስገባት የሚጥሩ ጥቂት የቀድሞ የህወሓት አመራር አባላትን ሕዝቡ በጋራ በቃችሁ ሊላቸው እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

አቶ ጌታቸው ረዳ እና የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ጋር በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት እያደረጉ ነው።

አቶ ጌታቸው በዚሁ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መፈረሙ ትግራይን የጦርነት አውድማ የማድረግ ፍላጎት ያላቸው አካላትን ምኞት ያስቀረ ነው ብለዋል፡፡

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በህገ-መንግስቱና በፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈናቃዮችን በሚፈለገው ልክ ወደ ቀያቸው መመለስ ያለመቻሉንም አንስተዋል።

ለዚህም በትግራይ ክልል በስልጣን ላይ ያለው ኃይል የሕዝቡን አጀንዳ ከማስቀደም ይልቅ ስልጣንና ስልጣን ብቻ በማለቱና እዚህ ግባ የሚባል ስራ ባለመስራቱ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በትግራይ ክልል አሁን የተፈጠረው ችግር የትግራይ ፖለቲከኞች የፈጠሩት መሆኑን በመግለጽ፤ አመራሩ የያዘው ግትር አቋም ትግራይ ከአደጋ ስጋት እንዳትወጣ እያደረጋት መሆኑን ተናግረዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ዓላማው ችግሮች በህገ-መንግሥታዊ አውድ እንዲፈቱ ማድረግ ቢሆንም፤ ከስህተታቸው የማይማሩት ጥቂት የቀድሞ የህወሓት ሀይሎች ለስልጣን ሲሉ ወደ ግጭት ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው እየገለጹ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአሁን ቀደሞ የተፈጠረው ግጭት የትግራይን ህዝብ ዋጋ እንዳስከፈለው የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ የትግራይ ህዝብ ተመሳሳይ ነገር እንዳይገጥመው የእነዚህን ሀይሎች እኩይ ፍላጎት እንዲያውቅ እያጋለጥን ነው ብለዋል።

በስልጣን መቀጠል የሚፈልጉ ጥቂት የአመራር ቡድኖች ልጆቻቸውን አስቀምጠው የደሀ ልጆችን ለእሳት እንደማገዱ በተግባር ያሳዩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህ ኃይል የእኔ ስልጣን ካልተረጋገጠ ሁሉም ነገር ገደል ይግባ የሚል መሆኑን ገልጸው፣ ዓላማውም ከተጠያቂነት ለማምለጥ መሆኑን አንስተዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰላም ፈላጊ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ ከተጠያቂነት ለማምለጥ ዳግም የትግራይ ህዝብን ወደ ግጭት ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረት ማጋለጥ ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ግንኙነት ከፌዴራል መንግስት ጋር መሆኑ ግድ ነው ያሉት አማካሪ ሚኒስትሩ፤ ከእከሌ ጋር ሆኜ ማጥቃት እችላለሁ የሚለውን ማጋለጥ አለብን ብለዋል።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን በትክክል ገቢራዊ ለማድረግ ከፌዴራል መንግስት ጋር ያለው ግንኙነት መጠናከር እንዳለበት ጠቅሰው፤ የትግራይ ህዝብ ለተወሰኑ ሰዎች የስልጣን ጥም መሞት የለበትም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት 99 በመቶ የሚሆነው አመራር ሰላም ፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህን ጥቂት የግጭት ጠማቂዎች በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.