በሲዳማ ክልል በበልግ እርሻ 152 ሺህ ሔክታር በሰብል ተሸፍኗል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሲዳማ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ152 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በሰብል ተሸፍኗል አለ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ፣ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ፋንታዬ ከበደ እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች በሀዋሳ ዙሪያ የተከናወኑ የበልግ እርሻ ልማት ሥራዎችን ተመልክተዋል፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በዚህ ወቅት ÷ በክልሉ በዘንድሮው የበልግ እርሻ ከ152 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በአጠቃላይ ከ24 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተናገሩት፡፡
በበልግ ወቅት ከሚለሙ ሰብሎች ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የበቆሎ ሰብል በ67 ሺህ ሔክታር ላይ መልማቱን አስረድተዋል፡፡
በጉብኝት መርሐ ግብሩ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
በጀማል ከዲሮ