ውይይት ለሀገራችን ወሳኝ ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለቀጣይ ትውልድ የተሻለችና የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ለማውረስ ሁሉም ሰው መተባበር እንዳለበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ ጠየቁ።
በወላይታ ሶዶ ከተማ እየተካሄደ ባለው በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ አቶ ጥላሁን ባደረጉት ንግግር፤ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት በዕድገት ጎዳና ላለች ሀገር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ጤናማ ፉክክር፣ ውጤታማ ትብብርና ገንቢ ምክክር ለሀገር ክብር መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልላችን ያሉ ሕጋዊ ዕውቅና ያላቸው 17 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብን ማዕከል አድርገው የመቻቻል ተምሳሌት የሆነ ፉክክር እያደረጉ ነው ብለዋል፡፡
መገፋፋት ማንንም አይጠቅምም፤ በመደመር እሳቤ ልዩነቶችን አቻችለን የተለያየ ርዕዮተ ዓለም ምልከታ ያላቸው ፓርቲዎችን በማቀራረብ በሐሳብ ልዕልና እንፎካከራለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የሰለጠነ የፖለቲካ አካሄድና ባሕል የዘመናችን ዓርበኝነት ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት ሰብሳቢ አቶ ጎበዜ አበራ ናቸው፡፡
ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ የመጣውን የተለያየ ሐሳብ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ የማሰባሰብ ልማድ በይበልጥ መጠናከር እዳለበትም አስረድተዋል፡፡
በመለሰ ታደለ