መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የባለ ራዕይ መሪ ማሳያ ነው – የአዘርባጃን አምባሳደር
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የአዘርባጃን አምባሳደር ሩስላን ናሲቦቭ መሶብ የአንድ አገልግሎት ማዕከል በፍጥነት ወደተግባር መግባቱ የቁርጠኛ እና ባለ ራዕይ መሪዎች ማሳያ ነው አሉ፡፡
አምባሳደሩ የአዘርባጃን የነጻነት ቀንን አስመልክቶ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ እንዳሉት፤ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ እና አዘርባጃን የሁለትዮሽ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በይበልጥ በትብብር መሥራት ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በዲጂታል አሥተዳደር እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ዕድገትም አድንቀዋል፡፡
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በፍጥነትና በተሳካ ሁኔታ መተግበሩን ጠቅሰው፤ ይህም ሀገራቸው ከተገበረችውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ካገኘው ‹‹አሳን ዲጂታል አገልግሎት›› ሞዴል ጋር ተመሳሳይነት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በአንድ ማዕከል የሚሰጠው አገልግሎት፤ የአገልግሎት ግልፅነትን ለማዘመን፣ ሙስናን ለመቀነስ እና የዜጎችን እርካታ በማሻሻል የበርካታ ሕዝባዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት ያግዛል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንም የማዕከሉን አገልግሎት የበለጠ ሲያውቁ የዲጂታል አገልግሎቱ ላይ ትልቅ ዕምነት ይኖራቸዋል ነው ያሉት፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የፐብሊክ ሰርቪስ ማሻሻያ እና ዲጂታል ትብብር ላይ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነት ሠነዶች ከተፈረሙበት ጊዜ ጀምሮ በቅርበት እየተሠራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኢትዮጵያዊት እና ከአዘርባጃናዊ አባት የተወለዱት ዕውቁ የጥበብ ሰው ሙጂራዲን በይላቃኒ በሀገራቱ መካከል የሕዝብ ለሕዝብ፣ ታሪካዊ እና የባህል ትስስር ምልክት መሆናቸውንም አስታውሰዋል፡፡
በመሳፍንት ብርሌ