የፍትህ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር የዘርፉ አስፈፃሚ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት የፍትህ ስርዓቱን ይበልጥ ለማጠናከር የዘርፉ አስፈፃሚ ተቋማት ቅንጅት ወሳኝ ነው ብለዋል።
19ኛው የፌዴራል እና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ “ማረሚያ ቤቶችን በአዲስ አስተሳሰብ ወደ አዲስ ምዕራፍ” በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ እየተካሄደ ነው።
አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በጉባኤው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የፍትህ ስርዓቱ ያሉበትን ችግሮች መፍታት የተቀናጀ አሰራር እንደሚፈልግ አስገንዝበዋል።
ተቋማት ቅንጅታቸውን በማጠናከር ተግባሮቻቸውን መከወን እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር የኑስ ሙሉ ማረሚያ ቤቶች የህግ ታራሚዎች ታርመዉ ህግ አክባሪ ሆነዉ የሚወጡበት ሥፍራ እንዲሆኑ በርካታ የሪፎርም ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።
ይህንን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የፍትህ ሚኒስትር ደኤታ ኡሙድ ኡጁሉ በበኩላቸው የፍትህ ዘርፍ በመንግስት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልጸው፤ በማረሚያ ቤቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተሻሽሏል ብለዋል።
ታራሚዎችን አርሞ እና አንጾ መልካም ዜጋ አድርጎ ለማውጣት በስፋት የተሰራ ቢሆንም ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የፍትህ አስፈጻሚ ተቋማት ይበልጥ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በሲሳይ ወርቁ