በአማራ ክልል የጎብኚዎችን ቆይታ ለማራዘም …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የጎብኚዎችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዓባይ መንግሥቴ እንደገለጹት፤ አሁን ያለው የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ በአማካይ 2 ነጥብ 5 ቀን ነው።
ይህን አሃዝ ለማሳደግ የሚያስችሉ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ቅንጅት እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት የመስኅብ ሥፍራዎች መንገድ፣ ውኃ፣ ኤሌክትሪክ እንዲሁም የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ደረጃ እና የምርት ጥራትን የማሻሻል ሥራ እየተሠራ መሆኑን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል በ19 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ወጪ የዘጌ ገዳማት የእግረኛ መንገድ እና በ25 ሚሊየን ብር የደቅ ደሴት የወደብ እና እግረኛ መንገድ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ ሰኔ ድረስ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ቢሮው 80 ሚሊየን ብር መመደቡን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶው በሕብረተሰቡ እንዲሸፈን በማድረግ የ41 ቅርሶች ጥገናና እድሳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ ካለፈው ዓመት አንጻር በዘርፉ ያሉ እንቅስቃሴዎች መሻሻል ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም በበጀት ዓመቱ ክልሉን የጎበኙት ሰዎች ቁጥር እና የተገኘው ገንዘብ ከዕቅድ በላይ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ለአብነትም በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት 8 ሚሊየን 688 ሺህ ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መምጣታቸውን እና ከዚህም 5 ነጥብ 29 ቢሊየን ብር መገኘቱን አረጋግጠዋል፡፡
በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፉ ለ23 ሺህ 560 ወገኖች ሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ነው ያስረዱት፡፡
በዮሐንስ ደርበው