በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 700 ዜጎች ተመልሰዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 700 ዜጎች እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል አለ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንደገለጹት÷በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እስካሁን ድረስ በማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 700 ኢትዮጵያውን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል።
አሁንም በማይናማር የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ኒው ዴልሂ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውክልና አለን በሚል በውጭ ሀገራት ስራ እናስቀጥራችኋለን እንዲሁም የትምህርት እድል እናመቻቻለን የሚሉ ሀሰተኛ ግለሰቦችና ተቋማት መኖራቸውን አመላክተዋል።
እነዚህን ሀሰተኛ ግለሰቦችና ተቋማት በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል ክትትል እንዲደረግባቸው እየተደረገ እንደሆነም ገልጸዋል።
ከውጭ ሀገራት የትምህርት እና የስራ ዕድል ጋር በተያያዘ በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚደረጉ ቅስቀሳዎች ኅብረተሰቡ እንዳይታለልም አሳስበዋል።
በመሳፍንት እያዩ