Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ አፍሪካ ፍልሰትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምስራቅ አፍሪካ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚከተሰተውን የሰዎች ፍልሰት ለማጥናትና ለመቆጣጠር የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል።

ፕሮጀክቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ አካባቢ ጥበቃ ማዕከል ኔትወርክ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን አስጀምሯል።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ እና አካባቢያዊ ጥበቃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር መኩሪያ አርጋው (ፕ/ር) በዚህ ወቅት÷ በምስራቅ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭቶች ምክንያት ከፍተኛ የሰዎች ፍልሰት መኖሩን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱም በቀጣናው የሚከሰተውን የሰዎች ፍልሰት ምክንያቶችን ለማጥናትና የጋራ ፖሊሲ በማውጣት ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

በምስራቅ አፍሪካ በዓመት ከ7 እስከ 10 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዘዋወሩ ገልጸው÷ ችግሩን ለመከላከል የጋራ ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀጣናው የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ በኬንያ የሚገኘው የዴንማርክ የስደተኞች ምክር ቤት፣ የጂቡቲ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ማህበር፣ የአውሮፓ ህብረት እና የዓለም አቀፍ የስደት ፖሊሲ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.