Fana: At a Speed of Life!

4 ሺህ ደንበኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቀቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፋር እና ጋምቤላ ክልሎች ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ከ4 ሺህ በላይ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፥ 400 ኪሎ ዋት አቅም ያላቸው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።

ተቋሙ ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እውን ለማድረግ የ25 የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነድፎ ከዋናው ግሪድ ርቀው የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎችንና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

በጋምቤላ ክልል የመተሃር ቀበሌ የተገነባው የፀኃይ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክት 558 ዋት ሶላር ፓኔሎች እና የኃይል እጥረት ቢያጋጥም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል 600 የባትሪ ሴሎችን በመጠቀም እስከ 250 ኪሎ ዋት ኃይል የመሰበሰብ አቅም ያለው ተጠባባቂ አውቶማቲክ ጀኔሬተር የተገጠመለት ነው፡፡

በተመሳሳይ በአፋር ክልል ባዳ ቀበሌ የተገነባው ፕሮጀክት 342 ዋት ሶላር ፓኔሎች እና የኃይል እጥረት ቢያጋጥም ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል 400 የባትሪ ሴሎችን በመጠቀም እስከ 150 ኪሎ ዋት ኃይል የመሰበሰብ አቅም ያለው ተጠባባቂ አውቶማቲክ ጀነሬተር አካቷል ነው ያሉት፡፡

ለፕሮጀክቶቹ በድምሩ 3 ነጥብ 98 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና 30 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የዝቅተኛ መስመር የተዘረጋ ሲሆን፤ ስምንት የተለያየ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮች የተገጠሙላቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶቹ የእውቀት ሽግግር እንዲኖር እና የስራ እድል እንዲፈጠር ጉልህ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል።

በተቋሙ እስከ አሁን በ25 የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እየተገነቡ የነበሩ በሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አጠቃላይ ሰባት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.