በክልሉ ለመኸር እርሻ የአፈር ማዳበሪያ እየቀረበ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለ2017/18 የምርት ዘመን መኸር እርሻ በቂ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትልና የግብዓት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አስራት አሰፋ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ ለአርሶ አደሩ በቂ የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል።
ከበልግ ወቅት የተረፈውን የአፈር ማዳበሪያ ለመኸር በመጠቀም የግብዓት እጥረት የመቅረፍ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸው÷ አሁን ላይ 103 ሺህ 705 ኩንታል የዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያ ለስርጭት ዝግጁ ሆኗል ብለዋል።
ለመኸር እርሻ የሚያስፈልገው ተጨማሪ 33 ሺህ 42 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በፌዴራል መንግሥት ግዥ መፈጸሙንና በቀጣይ ተጓጉዞ ወደ ክልሉ ይገባል።
የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ለማሟላት በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው፤ ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም የጥራጥሬ ሰብሎችን የማምረት ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ በስፋት መጠቀም የአፈር ለምነትን እያሳደገ መምጣቱንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም የክትትልና ድጋፍ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአድማሱ አራጋው