የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 46ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የመካከለኛ ዘመን 2018-2022 የማክሮ ኢኮኖሚ እና ፊሲካል ማዕቀፍ ላይ ነው፡፡ ማዕቀፉ የመንግስትን ገቢ መሠረት በማስፋት ወጪ ለመሸፈንና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ፣ ከመንግስት ገቢ አሰባሰብ እና ሀብት አመዳደብ አኳያ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በማመላከት ለቀጣይ በጀት አመት የበጀት ዝግጅት መነሻ ሆኖ እንዲያገለግል ማዕቀፉ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በማዕቀፉ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት እና ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተፈረሙ ሁለት የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ ነው፡፡ ከአረብ ባንክ የተገኘው 49,550,000 የአሜሪካ ዶላር ከግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር በማስተሳሰር ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ሲሆን አነስተኛ ወለድ የሚከፈልበት እና የ5 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ20 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ከዓለም ዓቀፍ የልማት ማህበር የተገኘው 45,100,000 ኤስ ዲ አር የሴቶች እና የልጃገረዶች ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚውል ሲሆን ከወለድ ነጻ፣ 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚከፈልበት እና 6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው፡፡ ምክር ቤቱም ብድሮቹ ከአገራችን የብድር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
3. ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚከፈል የአገልግሎት ክፍያን ለመወሰን የወጣ ደንብ ላይ ነው፡፡ ተቋሙ በዚህ ረገድ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያወጣውን ወጪ ሸፍኖ የውስጥ ገቢውንም ለማሳደግ እንዲችል የተገልጋዩን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ የአገልግሎት ክፍያ ለመወሰን ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
4. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በውጭ አገር ለስራ የሚሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች መብታቸው፤ ደህንነታቸው እና ክብራቸው በዘላቂነት መጠበቁን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲያስችል ሆኖ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
5. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የዕፅዋት ጥበቃና ኳራንቲን ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የተባይ አሰሳ እና ማስጠንቀቂያ ስርዓት ለመዘርጋት፤ ዕፅዋትን፣ የዕፅዋት ውጤትንና ሌላ ቁጥጥር የሚደረግበትን ቁስ በዓለም አቀፍ የዕፅዋት ጥበቃ ስምምነት መሰረት ተቆጣጥሮ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባትና ወደ ውጭ ለመላክ እንዲሁም ቁጥጥር የሚደረግበት ተባይ ከውጭ አገር ከገባ እንዳይስፋፋና እንዳይሰራጭ ለማድረግ እንዲያስችል ሆኖ ረቅቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡