Fana: At a Speed of Life!

የማሕበረሰብ አንቂዎችና ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በሀገራዊ ምክክሩ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በፌደራል ተቋማትና ማህበራት የምክክር ምዕራፍ የሚሳተፉ ተፅዕኖ ፈጣሪና የማህበረሰብ አንቂ ወኪሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ተጀምሯል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘገየ አስፋው በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ አለመግባባቶች የሚፈቱበት መንገድ የሠለጠነ ባለመሆኑ ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ ነው።

እንደ ሀገር መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ሰፊና መሠረታዊ መሆናቸውን አንስተው÷ አለመግባባቶች አንድነትን በመሸርሸር በጋራ ሰርተን ከድህነት እንዳንላቀቅ አድርገውናል ብለዋል፡፡

መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለመተማመን መነጋገር አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ ÷ ለዚህም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በምክክር ሒደቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ አለበት ነው ያሉት፡፡

ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና የማሕበረሰብ አንቂዎች ለምክክር ሒደቱ ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አስገንዝበዋል፡፡

ስለሆነም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት በመጠቀም በምክክሩ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክሩ ዋና ዓላማ የማያግባቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እውነትን በመፈለግ በመንግሥትና በሕዝብ እንዲሁም በሕዝብና ሕዝብ መካከል መተማመንን በመፍጠር አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር ነው።

ዛሬ የተጀመረው የተጽዕኖ ፈጣሪዎችና የማኅበረሰብ አንቂዎች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት ነገ በይፋ የሚጀምረው የተቋማትና ማህበራት የምክክር ምዕራፍ አካል መሆኑን የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.