የአየር ንብረት ለውጥ ጫና የስደት መንስኤ እንዳይሆን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዋነኛ የስደት መንስኤ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ለመመከት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ሰፊ ሥራ እየሰራች ነው።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያች የሚፈልሱ ወገኖች ቁጥር ጨምሯል።
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው ድርቅ እና ጎርፍ እንዲሁም ሰው ሰራሽ ግጭት ዜጎችን ለፍልሰት እየዳረገ መሆኑን አንስተው፤ ፍልሰተኞች ለችግር ተጋላጭ ሆነዋል ነው ያሉት።
በተለይም በስደተኞች ጣቢያ መሰረተ ልማት አለመሟላቱ ኢነርጂን ጨምሮ ወሳኝ ፍላጎቶች ላይ ተጽዕኖ ማስከተሉን ተናግረዋል።
ለአብነትም የኤሌክትሪክ አቅርቦት አለመኖር ፍልሰተኞች የማገዶ እንጨት ለመጠቀም እንደሚገደዱ ገልጸው፤ ይህ ደግሞ ከስደተኞች ተቀባይ አካባቢ ማህበረሰብ ጋር ግጭት ይፈጥራል ነው ያሉት።
በመሆኑም ፍልሰተኞችን ለማስተናገድ መሰረተ ልማትን ማሟላት ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ፍልሰተኞችን የሚያስተናግዱ ሀገራትን ለመደገፍ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለስደተኞች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ለስደት ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ለመመከት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አማካኝነት ሰፊ ሥራ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሚኪያስ አየለ