ፈረንሳይ በኢትዮጵያ ለንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ድጋፍ አደርጋለሁ አለች
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ከፈረንሳይ የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሉዊስ አንቶይን ሶሸ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የውሃና ኢኔርጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ጌትነት ጌጡ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ ውይይቱ በውሃ ልማት ፈንድ በኩል እየተተገበረ በሚገኘው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ላይ ትኩረት አድርጓል።
በዚህም የፈረንሳይ የልማት ድርጅት የከተሞች የውሃ አገልግሎት ተቋማትን አቅም ለመገንባት ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር እንደሚሰራ መግለጹንም አንስተዋል።
በውይይት መድረኩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የውሃ ልማት ፈንድ ስራዎችን ውጤታማነት ለማረጋገጥ የአደረጃጀት፣ የፕሮግራም አመራር እና አተገባበር ሂደቶች ላይ የላቀ አፈጻጸም ሊያመጣ በሚችል መልኩ እንደሚሰራ መግለፃቸውንም አመልክተዋል።
የከርሰምድር ውሃ ፍለጋ ጥናት ከምስራቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች ባሻገር በሌሎች መሰል ፕሮግራሞች ባልታቀፉ ሌሎች ክልሎች መተግበር እንደሚገባ ሚኒስትሩ ማንሳታቸውን ጠቁመዋል።
የፈረንሳይ መንግስት በኢነርጂ ልማት ዘርፍ፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በከርሰምድር ውሃ ጥናት ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ በውይይቱ ወቅት በድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተሩ ማረጋገጣቸውን አቶ ጌትነት ተናግረዋል።
የፈረንሳይ ልማት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ እና የጣሊያን የልማት ድርጅት በባስኬት ፈንድ ፕሮግራም በኩል በሚያደርገው ድጋፍ በሀገሪቱ 43 ከተሞች ላይ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አየተገነቡ መሆናቸውን አመላክተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ከ30 በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአድማሱ አራጋው