ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን በማረጋገጥ የትምህርት ጥራት የማሻሻል ስራ ይጠናከራል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማት ተደራሽነትን በማረጋገጥ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል አሉ።
በትምህርት ሚኒስቴር በጋምቤላ ከተማ ለሚገነቡ ሁለት ሞዴል የሁለተኛ ደረጃና አንድ የአዳሪ ትህምርት ቤቶች የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ደረጃቸውን የጠበቁ የትምህርት ተቋማትን ተደራሽ በማድረግ እንደ ሀገር የታለመውን የትምርት ጥራት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ሚኒስቴሩ ጋምቤላን ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ሞዴልና የአደሪ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ ወደ ትግበራ ምዕራፍ መግባቱን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ከተማ የሚገነቡት ሁለት ሞዴልና አንድ አደሪ ትምህርት ቤቶች ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘላቸው ገልጸው÷ ወጪው በትምህርት ሚኒስቴርና ሰዎች ለሰዎች በተሰኘ ግብር ሰናይ ድርጅት የሚሸፈን መሆኑን አስረድተዋል።
የትምህርት ቤቶቹ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቁ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው÷ የአንድ ሀገር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ሊፋጠን የሚችለው ብቃት ያለውና ተወዳደሪ ዜጋ ማፍራት ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የተማሪ ክፍል ጥምርታን ማመጣጠን ሲቻል መሆኑን አንስተው÷ ሚኒስቴሩ በክልሉ የትምህርት መሰረተ ልማት በማሻሻል በከተማው ሞዴል ትምህርት ቤቶችን በመገንባት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።