የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፉን በንግግር የከፈቱት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)÷ ለችግሮቻችን መፈጠር መሰረት የሆኑ ችግሮችን በጋራ ተነጋግሮ መፈለግ ባለመቻሉ ያለመግባባት ቋጠሮዎች ሳይፈቱ ዓመታትን ተሻግረዋል ብለዋል።
ተሳታፊዎች ድህነት እና ኋላ ቀርነት ለመነሳት እየታገለች ያለችውን ኢትዮጵያ በጸና ሰላም ላይ ለማቆም የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችሉ ገንቢ ሃሳቦችን ማዋጣት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።
የሀገራዊ ምክክሩ ተቀርጾ ወደ ስራ ሲገባ በሌሎች ሀገራት የነበሩ በጎ ተሞክሮዎችንም ጭምር በመቀመር ለውጤታማነቱ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ እና በምክክሩ ያልተሳተፉ ሀይሎች ጭምር በጋራ ሀሳብ የጸና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዛሬው የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር መርሐ ግብር መካሄድ በኋላ በቀረው የትግራይ ክልልም አጀንዳ ማሰባሰብ ይካሄዳል ተብሏል፡፡
የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ምክክር ሂደት የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መምህራን፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በአጠቃላይ ከ38 ተቋማት የተውጣጡ ከ850 በላይ ወኪሎች እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እስካሁን ከ11 ክልሎች እና ከ2 ከተማ አስተዳደሮች በድምሩ ከ1 ሺህ 120 ቀባሌዎች የተሰበሰሰቡ 13 የአጀንዳ ሰነዶችን የማሰባሰብና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ ተጠናቋል፡፡
በይስማው አደራው