Fana: At a Speed of Life!

አንድ ዕቅድ፣ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አንድ ዕቅድ፣ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የአባይ ተፋሰስ የሲቪክ ማህበራት ሚና በሚል መሪ ሃሳብ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያውያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ወዳጆች ርብርብ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ የደረሰውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል በመጠበቅ ከትውልድ ትወልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ያለመ ነው።

መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ የምርምር ተቋማትና ማህበረሰብን ባሳተፈ መልኩ ሳይንሳዊ ዕቅድ ለማዘጋጀት ያግዛል።

በዚሁ ወቅት የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የግድቡ ግንባታ ሂደት ባለፉት 14 ዓመታት የገጠሙትን በርካታ ተግዳሮቶች አልፏል።

በዚህም መንግስት እና በህዝብ ተሳትፎ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የይቻላል መንፈስን መፍጠሩን አንስተው፤ በዚህ ስሜት በርካታ ተጨማሪ ሀገራዊ ስኬቶችን ተጎናፅፈናል ብለዋል።

በገንዘብ፣ በሞራል፣ በጉልበት እና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ የተፈጥሮ ሃብታችንን የመጠቀም መብታችንን እውን እንዳደረግነው ሁሉ በተፋሰስ፣ በውሃና መሬት ጥበቃ ስራ ልንደግመው ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.