የሉሲና የሰላም ቅሪተ አካል በደሴ ሙዚየም ከነገ ጀምሮ ለእይታ ይቀርባሉ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከበርባት ደሴ ከተማ የሉሲና የሰላም ቅሪተ አካል በደሴ ሙዚየም ከነገ ጀምሮ ለእይታ ይቀርባሉ፡፡
የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን የብሄራዊ ሙዚየም መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አንዷለም ግርማይ እንደገለፁት፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከደረሰበት ጉዳት ለመታደግ እድሳት የተደረገለት ደሴ ሙዚየም ከነገ ጀምሮ በከፊል ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል፡፡
ሙዚየሙ በነገው ዕለት አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የሰው ዘር መገኛ ምስክር የሆኑት የሉሲና ሰላም ቅሪተ አካላት በጉብኝቱ ይካተታሉ ብለዋል፡፡
የደሴ ሙዚየም ጥንታዊ ቅርሶቹን በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ማጣቱን አስታውሰው፤ በተለያየ አጋጣሚ ቅርሶቹ እጁ ላይ የገባ አካል አካል ወደ ቦታቸው እንዲመልስ ጥሪ አስተላልፈዋል።
ጎብኚዎች ከነገ ከሰአት ጀምሮ እስከ ማክሰኞ ምሽት ሉሲ እና ሰላምን ጨምሮ በሙዚየሙ ያሉ ጥንታዊ ቅርሶችን መጎብኘት ይችላል ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ናቸው።
ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ48ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ23ኛ ጊዜ ከግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በደሴ ከተማ ይከበራል።
በሰብለ ሲሳይ