ሰው ወደፈለገበት ቦታ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል – ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ሰው ወደፈለገበት ቦታ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።
ኮሚሽነር ጀነራሉ ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ከዕገታ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የከተተውን ሁኔታ ለመቀየር ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከደህንነት ተቋማት እና ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በስፋት ተሰርቷል።
በዚህም ችግሩን በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸው፤ በዕገታ ድርጊት የሚሳተፉት አሸባሪው ሸኔ፣ ጽንፈኛው ፋኖ እንዲሁም በእነዚህ አካላት ስም የሚንቀሳቀሱ ዘራፊ ቡድኖች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
በገጠር እና በከተማ አካባቢ ዜጎችን በማገት ከቤተሰቦቻቸው ስልክ መደወልን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ገንዘብ የሚጠይቁበት እና የሚወስዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር አስታውሰው፤ በተሰራው የተቀናጀ ኦፕሬሽን ዕገታን ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
ይህንን ሁኔታ ለማስቀረት በተሰሩ ኦፕሬሽኖች በዕገታ ተግባር ይሳተፉ የነበሩ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በተለያየ መንገድ የዘረፉት በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በባንክ እንዲታገድ መደረጉን የገለጹት ኮሚሽነር ጀነራሉ፤ የምርመራ ሂደቱ ሲጠናቀቅ በድርጊቱ ጥቃት ደርሶባቸው የተዘረፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ገንዘባቸውን የሚያገኙበት መንገድ በምርመራ እየታየ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በዕገታ ወንጀል ላይ የተሰማሩትን በቁጥጥር ስር እያዋልን ተጠያቂ እያደረግን ነው በማለት ገልጸው፤ በተለያየ ጊዜ ዕገታም ግድያ ሲፈጽሙ እንደነበር ተጠርጥረው የተያዙ ጉዳያቸው በምርመራ እየተጣራ መሆኑን አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከዕገታ ጋር በተያያዘ የሚሰማ የወንጀል ድርጊት ብዙ እንዳልሆነ ጠቅሰው፤ የፌዴራል ፖሊስ በአራቱም ማዕዘን የፈጥኖ ደራሽ እና የኮማንዶ ኃይል ስምሪት በመስጠት ቅኝት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም መንገዶቻችን በየትኛውም መልኩ በጣም የተሻሉ እና ሰው ወደፈለገበት ቦታ መንቀሳቀስ የሚችልባቸው ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።