Fana: At a Speed of Life!

በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የተራቆተ አካባቢን ለማልማት ጥናትና ምርምርን መከተል ይገባል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የተራቆተ አካባቢን ለማልማት ጥናትና ምርምርን መከተል እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ አሳሰበ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ጉድለት የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ የማድረግ ስራ በጥናትና ምርምር ተደግፎ እየተከናወነ ነው።

በዚህም በወላይታ ዞን በዳሞት ወይዴ ወረዳ ቶራ ሳዴቦ ቀበሌ በተመረጡ የውሃ እቀባ መንገዶች፣ በእጽዋት ጽድቀትና የቦረቦር ቦታዎች ማገገሚያ ዘዴዎችን በመከተል ለድርቅ ተጋላጭ በሆነና ነዋሪዎችን ለስደት እየዳረገ የነበረውን መሬት መልሶ ማልማት ተችሏል።

በወረዳው በ19 ተፋሰሶች የአካባቢውን መልክአ ምድር አቀማመጥን ያማከለ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ላለፉት ሁለት አመታት በጥናት መሠረት ባከናወናቸው ሥራዎች የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ አረንጓዴ ማልበስ መቻሉን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዮት መብራቴ (ዶ/ር) ገልፀዋል።

የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ገነነ ገዛኸኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው የተራቆቱ ቦታዎችን በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከም እንዲሁም ቴክኖሎጂ በመጠቀም የመጣውን ለውጥ ለሌሎች አካባቢዎች እንደ ማስተማሪያ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የወላይታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ ዳንኤል ዳሌ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ከዚህ በፊት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይሰደዱ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች በተሰራው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ተረጋግተው እያለሙ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዳሞት ወይዴ ወረዳ ቶራ ሳዴቦ ቀበሌ መልክአ ምድሩ ለተለያዩ የግብርና ስራዎች የሚመች ስለሆነ በቀጣይ አርሶ አደሩ ተጠቃሚ የሚሆንባቸው የንብ ማነብና መሠል ሥራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

አካባቢው ገላጣ ስለነበረ በዝናብ ወቅት ለጎርፍ አደጋ ከመጋለጥ ባሻገር ለም አፈር ተጠራርጎ በመወሰዱ ለድርቅ እየተዳረጉ እንደነበር የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት አውስተዋል።

የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል በተፈጥሮ እንክብካቤ ሥራው ህብረተሰቡን በማሳተፍ በመጣው ለውጥ ተስፋቸው መለምለሙን ተናግረዋል።

በመለሰ ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.