Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የተለያዩ አዋጆችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 33ኛ መደበኛ ስብሰባ ሁለት የብድር ስምምነቶችን ጨምሮ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅን መርምሮ አፀደቀ፡፡

የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ እና በዓረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት መካከል ለተቀናጀ የውጤታማ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ለወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የተደረገውን የብድር ስምምነት አዋጅ አስመልክቶ አብራርተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም፤ የብድር ስምምነቱ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለማስፋፋት፣ የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባት፣ የመስኖ አውታሮችና እና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ወጣቶች በግብርና ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ስምምነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለሴቶች እና ልጃገረዶች ጤና የተቀናጀ፣ ጠንካራ፣ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የቀረበውን የብድር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበ አዋጅን አስመልከቶም ገለጻ አቅርበዋል፡፡

ስምምነቱ በጤናው አገልግሎት ዘርፍ ጥራት እና ተደራሽነትን ለማስፋት፣ በሴቶች ቅድመ ወሊድ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ምቹ የጤና ተቋማትን ለመገንባት እና የጤናውን ዘርፍ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ስምምነት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ምክር ቤቱም የብድር ስምምነት አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅን ቁጥር 1383/2017 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡

በእዮናዳብ አንዱዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.