Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ይቀጥላል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መንግሥት ለሰላም እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪና ልማት የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ 3ኛውን “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄ ኤክስፖ መርቀው ከፍተዋል።

አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኤክስፖው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ ጎንደር እንደሀገር ልዩ ትኩረት በተሰጠው የአምራች ዘርፍ ልማት ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል በችግር ጊዜም የልማት አርበኛ ሆኖ ለመቀጠሉ ጎንደር ምስክር ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የትናንት፣ የዛሬና የነገ ሥልጣኔ መገናኛ የአምራች ኢንዱስትሪ ኮሪደር እየሆነች መሆኗንም ገልጸዋል።

ጎንደር እንደ አዲስ እየተወለደች፣ እየተሠራች፣ እየፈካች ናት ያሉት አቶ ተመስገን÷ ሕዝቡም ከፍተኛ የልማት ፍላጎት እንዳለውና ከዚህም የሚያደናቅፈውን እንደማይፈልግ ገልጸዋል።

በኤክስፖው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበልን ጨምሮ የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.