አማራ ክልልን በአምራች ዘርፍ በማሳደግ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት እንሥራ- አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በወጣቶች እና በመልማት አቅም ሃብታም የሆነው አማራ ክልልን በአምራች ዘርፍ በማሳደግ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገት ልንሠራ ይገባል አሉ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ።
3ኛው የአማራ ክልል የ “ኢትዮጵያ ታምርት፤ እኛም እንሸምት” ኤክስፖ ማጠቃለያ በጎንደር ከተማ ተከናውኗል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኤክስፖው በሁሉም ዞኖች ይህንን ዓመት ጨምሮ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት ሲከናወን ቆይቷል።
በተጨማሪም ኤክስፖው በክልሉ የልማት አቅሞች እና ጉድለቶች እንዲሁም የቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይም ሲመክር መቆየቱን አውስተዋል፡፡
በመሆኑም በታቀደው እና በምንፈልገው ልክ ባይሆንም ለውጥ እየተመዘገበ ነው ብለዋል በንግግራቸው።
ዘርፉ አሁንም ልዩ ትኩረት ይፈልጋል ያሉት አቶ አረጋ፤ የመምራት ብቃትን ጥራት እና ፍጥነት ባለው ውሳኔ በማጀብ መሥራት እንደሚጠበቅ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
የቅንጅት ጉድለትን ማስተካከል እና ቀልጣፋ አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡
በፋይናንስ፣ በሰው ኃይል እና በጥሬ ዕቃ አቅርቦት በማሳደግ አምራች ዘርፉን በምርምር ማሳደግ የቀጣይ ሥራችን ነው ሲሉ አመላክተዋል፡፡
በክልሉ የታየው ግጭት ያስከተለው የሃብት ጥፋት፣ የእንቅስቃሴ መሥተጓጎል በታቀደው ልክ እንዳንፈጽም አድርጎናል ብለዋል አቶ አረጋ።
አቅሞችን እንዲሁም የተቋማት ግንባታን በማጠናከር የንግድ ሚዛንን ለማስተካከል እና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ልማት ልንሠራ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ አቅም ገና በበቂ መጠን ጥቅም ላይ እንዳልዋለ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ ናቸው፡፡
ችግሩን በመለየት እና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመቅረጽ መሠረተ ልማትን በማሟላት ሃብቱ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በለይኩን ዓለም