ጎርፍ በማስከተል ስጋት የነበረው ውሃ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምሯል – ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ሲንቢጣ ቀበሌ ጎርፍ በማስከተል ስጋት የነበረው ውሃ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምሯል አሉ፡፡
በዞኑ በመስኖ የሚመረቱ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎች በተደጋጋሚ በጎርፍ አደጋ ሲጋለጡ የነበሩ የአካባቢውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎች ከ5 ዓመታት በፊት ከውጪ በዶላር ሲገቡ የነበሩ መሆናቸውን አስታውሰው÷ አሁን ላይ በስፋት በመመረት ወጣቶች እና አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ምርቶቹ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉና ኤክስፖርት በማድረግ የውጪ ምንዛሪን የሚያስገኙ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
አቮካዶው ትክክለኛ ርቀቱን ጠብቆ በመተከሉ አርሶ አደሩ አቮካዶ ፍሬ እስኪሰጥ በቆሎን ጨምሮ ሌሎች ሰብሎችን በመዝራት ምርት ማግኘት እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
በዞኑ የታየው ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ልምዱን በሌሎች አካባቢዎችም በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም የውጪ ምንዛሬን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው ዕለት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን ዌራ ዲጆ ወረዳ ሲንቢጣ ቀበሌ የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆኑ ሞዴል የገጠር መንደሮች ግንባታን ማስጀመራቸው ይታወቃል።
በአቤል ንዋይ