Fana: At a Speed of Life!

ጽዱ ኢትዮጵያን የዜጎች ባሕል ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጽዱ ኢትዮጵያን የማረጋገጡና የዜጎች ባሕል የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን።

የባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) እንዳሉት፥ 2ኛው ዙር ሀገራዊ የብክነት ቅነሳ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።

ንቅናቄው ለ6 ወራት የሚካሄድ ሲሆን፥ የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ህግ መከበሩን ማረጋገጥና መልካም ተሞክሮ ያላቸው አካላትን እውቅና መስጠት ላይ ያተኩራል ብለዋል።

በንቅናቄው በፕላስቲክ እንዲሁም በውሃ እና አፈር ብክለት ማለትም በመጤ አረሞች እና የአፈር አሲዳማነት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል።

በተጨማሪም አየር ብክለትን በተለይም የመኪና ጭስን ለመከላከል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማሳደግ ግንዛቤ መፍጠር ላይ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

ገጠራማ አካባቢዎችን ከብክለት ነጻ የሆነና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የተጀመረውን የገጠር ኮሪደር ልማት ለማጠናከር እንደሚራ አንስተዋል።

የድምጽ ብክለት መከላከል እና የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ በተለይም አደገኛ ኬሚካል ክምችቶችን በአግባቡ ማስወገድ ላይ ይሰራል ብለዋል።

በንቅናቄው 15 ሚሊየን ዜጎችን ቀጥተኛ ተሳታፊ ለማድረግ መታቀዱንም ነው ያብራሩት።

ጽዱ የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉም ማህበረሰብ የበኩሉን ኃፊነት እንዲወጣም ጠይቀዋል።

ጽዱ ኢትዮጵያን የዜጎች ባህል ለማድረግ የሚደረገውን ሒደት ለማሳለጥ እስካሁን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን ጨምሮ አራት ህጎች መሻሻላቸውን ጠቁመዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.